አወዛጋቢው የአወልያ ት/ቤት እና የልማት ድርጅት በቦርድ እንዲተዳደር ተወሰነ

(አዲስኒውስ) አዲስ አበባ – ላለፉት ሶስት ዓመታት እያወዛገበ ያለው የአወልያን ትምህርት ቤት እና ልማት ድርጅት ማን ያስተዳድረው የሚለው ጥያቄ መፍትሄ እንደተገኘለት ትላንት ለጋዜጠኞች በተሰጠ መግለጫ ተገለጸ:: ከዚህ በፊት በቀድሞ የእስልምና ምክር ቤት ውሳኔ የአወልያን የልማት ድርጅት ያስተደደር የነበረው አለም ዓቀፉ የእስልምና ድርጅት ሲታገድ የልማት ድርጅቱ በምክር ቤት እንዲተዳደር መደረጉ የሚታወስ ሲሆን ህዝበ ሙስሊሙ ይህንን ውሳኔ በመቃወም ከፍተኛ የሆነና ሰላማዊ ተቃዉሞውን ላለፉት ሶስት ዓመታት ሲያሳዩ ቆይተዋል፡፡

ከተቃውሞው በተጨማሪ ኮሚቴዎች በመምረጥ በአወልያ ጉዳይ እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ ጋርም ውይይቶችን ጀምረው እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህም ባለመሳካቱ እና በህዝበ ሙስሊሙ የተመረጡት የሰላም አፈላላጊ ኮሚቴዎች በመንግስት ቁጥጥር ሲውሉ ተቃወሞ በከፍተኛ ሁኔታ እንደተባበሰ እና የአውልያ ትምህርት ቤት በእስልምና ምክር ቤት መተዳደር የለበትም፣ የአወልያን የልማት ድርጅት ነፃ የሆነ ገለልተኛ ወገን ሊመራው ይገባል፣መጂሊሶቹ አይወክሉንም፣ የታሰሩት የሰላም አፈላላጊ ኮሚቴዎች ይፈቱ የሚል የተቃውሞ ድምጾችን ላለፉት ሶስት ዓመታት እያሰሙ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በቅርቡም በታላቁ የአኑዋር መስጊድ ህዝበ ሙሰሊሙ ከጸሎት(ሶላት) ቦኃላ ተቃውሞቻውን እያሰሙ ባለበት ቅት በመንግስት ሀይሎች ከፍተኛ የሆነ ድብደባ እና እስር እንደተፈጸመባቸው በተለያዩ የዜና ዘገባዎች እና ማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የወጡት ምስሎች ያሳያሉ፡፡

Ethiopian-Muslim-Protesters-in-Addis-Ababa

በትላንትናው ዕለት የእስልምና ምክር ቤቱ ፕረዝዳንት የሆኑት ሼክ ኪያር መሀመድ አማን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የአወልያ ጉዳይ መፍትሔ ማግኘቱን ገልጸዋል፡፡ የአወልያ ጉዳይ ተቃውሞ ያስነሳው የቀድሞ የምክር ቤቱ አመራሮች በአወልያ ትምህርት ቤት መምህራን እና ተማሪዎች ላይ የህዝቡን ስሜት ባለመረዳት በወሰዱት ተገቢ ያልሆነ እርምጃ ምክንያት ተቃውሞ ሊነሳ ችሏል ብለዋል፡፡ አያይዘውም በአሁን ጊዜ ግን በህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄ መሠረት አወልያ በቦርድ እንዲተዳደር ሆኗዋል ብለዋል፡፡ ቦርዱም የእስልምና እውቀታቸውን እና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ባላቸው ምሁራን፣ ባለሀብቶች እንዲሁም ከክልል እና ከፌዴራል የእስልምና ምክር ቤቶች በተወጣጡ ሰዎች ቦርዱ መመሥረቱን ገልጸዋል፡፡

የእስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት በዓመት ከ7 ሚሊዮን ብር እሰከ 10 ሚሊዮን ብር መድቦ ለመምህራን ደሞዝ እና ለትምህርት ቤት ወጪ እንደሚያደርግ ሲገለጽ በአሁኑ ውቅትም የአወልያ ልማት ድርጅት ዓመታዊ በጀቱ 20 ሚሊዮን ብር እንደተደረገ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የአወልያ የልማት ድርጅት በውስጡ ጤና ጣቢያ ፣ትምህርት ቤት እና ሌሎች ተቋማት ያሉት ሲሆን በትምህርት ቤቱም 2500 ለሚሆኑ ተማሪዎቸ ትምህርት ይሰጣል፡፡ ከነዚህም ተማሪዎች 500 የሚሆኑትን በነፃ የሚያስተምር ሲሆን ከ125 ተማሪዎቹ ደግሞ ግማሽ ክፍያን ሲቀበል ከቀሩት ተማሪዎች ግን ሙሉ ክፍያውን ይቀበላል፡፡

የአልያ የልማት ድርጅት በቦርድ እንዲተደደር ከእስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት መወሰኑን እንዴት እንደተመለከተው ጥያቄ ያቀረብኩለት የቀድሞ የአውልያ ትምህርት ቤት ተማሪ የነበረው ሰኢድ  “መጅሊሱ/ምክር ቤቱ ይህን ውሳኔ ለመወሰን በጣም ዘግይቷል ቢሆንም አውልያ በቦርድ እንዲተደደር መወሰኑ እንዳስደሰተው ተናግሯል፡”፡ ሌላው አሰተያየቱን የሰጠኝ የአወልያ ተማሪ የነበረና በረብሻው ምክንያት ትምህርቱ እንዳቆም የነገረኝ መኑር የተባለ አሰተያየት ሰጪ “ይሕ ውሳኔ የመጀሊሱ ሳይሆን የመንግስት ነው፡፡ ምክንያቱም መጀመሪያም መንግስት ነው ይህ ሁሉ እንዲፈጠር ያደረገው አሁንም ሁኔታዎችን መቆጣጠር ሲያቅተው ለማረጋት እና ህዝበ ሙስሊሙ ለጥያቄያቸው መልስ አግኝተዋል ብሎ ለማውራት እንዲመቸው ያደረገው ነው ፡፡” ሲል የግል አሰተያየቱን ለአዲስኒውስ ሰጥቷል፡፡
 
የሆነው ሆኖ ከህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የሆነው የአወልያ ጉዳይ በቦርድ እንዲተዳደር ተወስኗል፡፡ በእርግጥ ህዝብ ሙስሊሙ ይህን ውሳኔ ተቀብሎታል? ተቃዎሞንስ በዚህው ያበቃል? እርስዎስ ይህ ውሳኔ የሙስሊሙን ጥያቄ ይፈታል ወይስ ሌላ የመንግስት ማረጋጊያ ዘዴ ነው ብለው ያስባሉ? እነዚህ ጥያቄዎች በሚመጡት የጁማዓ ቀናት መልስ የምናገኝላቸው ይሆናሉ፡፡

የእርስዎን አስተያየት ከዚህ በታች ባለው አስተያዬት መስጫው ላይ ያስፍሩ::

See Also:  Ethiopia's crackdown on dissent drives opposition to push for 'Freedom First'


AddisNews is not responsible for the contents or reliability of any other websites to which we get contents from and provide a link and do not necessarily endorse the views expressed by them.

Related posts

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Share to Friends

Send this to a friend