መምህር ግርማ ወንድሙ አዲስ የተጠረጠሩበት ወንጀል ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መምህር ግርማ ወንድሙ አዲስ የተጠረጠሩበት ወንጀል ይፋ ሆነ።

ይህ የተጠረጠሩበት ወንጀል ሀሰተኛ ሰነድ መገልገል የሚል ነው ብሏል የአዲስ አበባ ፖሊስ።

ጥቅምት 23 2008 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ባልሰጠኋቸው የስብከት እና የማጥመቅ ፈቃድ እንደሰጠኋቸው በማስመሰል በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር በቤተክርስቲያኒቱ ስም ሲያስተምሩ እና ሲያጠምቁ ቆይተዋል በማለት ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በፃፈው ደብዳቤ አሳውቋል።

ይህንን በተመለከተም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ያለ ቤተክርስቲያኒቱ እውቅና በህገ ወጥ መንገድ በሀሰተኛ ሰነድ ተጠቅመው ሲያገለግሉ ነበር በማለት ለመምህር ግርማ ወንድሙ የተፃፉ ሰባት ቅፅ ደብዳቤዎችን ጠቅላይ ቤተክህነት ለፖሊስ በመሸኛ ደብዳቤ ልኳል።

Memehir_Girma_Wendimu_facebook

በዚህ መሰረት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የምርመራ ቡድን ይህንን ምርመራ ለማከናወን 14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል።

ተጠርጣሪው መምህር ግርማ ወንድሙ በበኩላቸው ደቡብ ወሎን ጨምሮ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ቤተክህነት ደብዳቤ እየፃፈልኝ ነው ሳገለግል የሰነበትኩት ብለዋል።

ጠበቆቻቸውም እንዲሁ ሌላው ቢቀር እሳቸው በቋሚነት በሚያገለግሉባቸው የረር ስላሴ እና ጀሞ ሚካኤል እንኳን ህገ ወጥ ናቸው የሚል በቤተክህነት የተላከ አንዳችም ደብዳቤ ያለመኖሩን እንዲሁም መንፈሳዊ አገልግሎት መስጠት ወንጀል ስላልሆነ ፍርድ ቤቱ የተጠየቀውን የጊዜ ቀጠሮ አቤቱታ ውድቅ አድርጎ ደንበኛችን የዋስትና መብታቸው ይከበርላቸው ሲል ጠይቋል።

የምርመራ ቡድኑ በበኩሉ የተጠረጠሩበት ወንጀል ሀሰተኛ ሰነድ መገልገል በመሆኑ ችሎቱ የጠበቆቹን ጥያቄ እንዳይቀበል ሲል አመልክቷል።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀን የ7 ቀኑን ፈቅዷል።

ውጤቱን ለመጠባበቅ ለህዳር 3 ቀን 2008 ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

በሌላ በኩል መምህር ግርማ ወንድሙ ባለፈው ሳምንት ከተጠረጠሩበት የማታለል ወንጀል ጋር በተያያዘ ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ስራ አለኝ በማለት ከጠየቀው 14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤቱ አምስት ቀን ብቻ ነው የፈቀደው።

ፖሊስ ድጋሚ ቀነ ቀጠሮ ለመጠየቅ ካቀረበው ምክንያት መካከል ያልተያዙ ተጠርጣሪዎች አሉ፤ ከቤት ሽያጭ ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪው ከሚኖሩበት ወረዳ የሰነድ ማስረጃ አልቀረበልኝም፤ ቤታቸው ላይ በተደረገው ብርበራ ስምንት ሲም ካርዶች የተገኙ በመሆኑ ሲም ካርዶቹ በማን ስም የወጡ ናቸው? እና በስልኩ ውስጥ የሚገኙ መረጃዎችን ኢትዮ ቴሌኮም አጥርቶ እንዲልክልን ደብዳቤ ፅፈን ውጤቱን እየተጠባበቅን ነው የሚሉት ይገኙበታል።

በዚህም ላይ የተጠርጣሪው ጠበቆች ሰው ታስሮ ሌላ ሰው ለመያዝ በሚል ተጨማሪ ቀን ሊጠየቅ አይገባም፤ ህጉም አይፈቅድም፤ እና ፖሊስ ምርመራውን ቀደም ሲል ያጠናቀቀ በመሆኑ ባለፈው በተሰጠው 7 ቀን የተጠርጣሪውን ቃል ተቀብሎ ክስ መመስረት ሲገባው ደንበኛችን ያለአግባብ እየታሰሩ ነው ብለዋል።

ችሎቱ ከኢትዮ ቴሌኮም የሚመጣውን መረጃ ለመጠባበቅ ከተጠየቀው 14 ቀን 5 ቀን ብቻ ፈቅዷል።

የዚህንም ውጤት ለመጠባበቅ ለጥቅምት 30 2008 ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።


AddisNews is not responsible for the contents or reliability of any other websites to which we get contents from and provide a link and do not necessarily endorse the views expressed by them.

Related posts

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Send this to a friend